ቤባንያ ገፅ ፱

December 25, 2023

“እኔና አንቺ?”ጅል’ ሳቅ ፈለቀች፣ አሳዘንኳት፤ አፌ ላይ ሳመችኝ። ምንድነው ተአምሩ? ከንፈሬና ልቤን የሚያገናኝ ምን መስመር ተዘርግቷል? መቼ ይሆን ዳግም የምትስመኝ?“ኧረ ሸኖዎች። ብዙ ደራሲዎቻችን የተወለዱት እኛ ዙሪያ ነው። አለቃ ደስታ ተክለወልድ እዚህ ጎሽ ውሃ ነው የትውልድ መንደራቸው:: ተክለጻድቅ መኩሪያ ሣር አምባ የሚባል ቦታ ነው የተወለዱት:: ብዙ የታሪክ መጽሐፍ አበርክተውልናል። እ. . . ፊታውራሪ ተክለሀዋርያት ተክለማሪያምም ሳያ ደብር በዚህ አቅጣጫ ነው የትውልድ መንደራቸው…”ምን ስትል ይሄን ሁሉ አጠናችው? አሰብኩ::ታድለንዝም!“ወደፊት ትልቅ ሆቴል ሸኖ ላይ አቋቁሞ መነሻ በማድረግ የሁሉንም ደራሲዎች የትውልድ ሥፍራ ማስጎብኘት::””ከዚያስ?” ሳላውቀው ጠየቅሁ“ከዚያማ የፃፉትን እያስተዋወቁ፣ እየተነተኑ እንግዶችን ሁሉ ታሪክ ተቀባይ ማድረግ።”እኔን የከበደ ሚካኤል ታሪክ ተቀባይ እያደረገች ይሆን? እነዚያንስ? እሷ ዘንድ ስለደራሲዎቹ ለማወቅ ሲመጡ እንደእኔ ጭጋግ አከናንባ ጭኗን አንተርሳ ይሆን ግጥም የምታነብላቸው? ቅናት!! ከተንጋለልኩበት ጭኗ ተነስቼ ቁጭ አልኩ:: እምብዛም ወደማያወላዳው የማዶ እይታ ቀልቤን ሰጠሁ፡፡ ጭጋግ፤ የአካባቢ መበላሸት ይሆን?“የራስህ ጉዳይ?” ተነስታ ቀሚሷን ወደታች ዠለጠች፡፡ ጉንጯ ቀልቷል፤ ፊቷ ወደ ሐምራዊ የሚያደላ ቀለም ፈሶበታል። ( ግን ሐምራዊ እንዴት ያለ ቀለም ነው?)“እንጃ !””ልንሄድ ነዉ? ““አንተ ቆይ እኔ እሄዳለሁ!”በእናትሽ…..”ምን?””እንደዚህ አትሁኚ… ይጨንቀኛል””አንተ የምትሆነው ይታወቅሃል?”እንደ አዳምና ሄዋን የፍጡር መጀመሪያነት፣ የፍጡር ብቸኛነት ተሰማኝ፡፡ ሄዋን ከሄደች ከአጋዘኑ፣ ከጎሹ፣ ከጉርጡ ከምስጡ፣ ከአንበሳው፣ ከጥንብ አንሳው… ውጭ ለአዳም ማን አለው?“እሺ ይቅርታ!”ቁና ቁና ተነፈሰች፣ ለሄዋንስ ማን አላት? አዳምን ጥላ የት? አብሯት ሲኳትን የሱሪውን ጫፍ የጭቃ ጥለት የተጠለፈበት ግፍ አይሆንባትም?ቁጭ አለች።

ክፍል 5

hማና የራስ ምስልሆሴዕ የእንጨት በርሜሉ ላይ የተቀጣጠለ ኩራዝ አስቀምጧል። የኩራዙ ፍቺ አልጠፋኝም። እንደ ዲዮጋን በፀሐይ ብርሃን ኩራዝ ይዞ ወጥቶ፡-“ምን ትፈልጋለህ?” ሲሉት“ሰው!” ሊል ነው። ሰው! በብርሃን ተፈልጎ የጠፋ፤ ሰው። እነ አርስቶትልና እነ ፕሌቶ ሁሉ ለተሳዳቢው ዲዮጋን “ሰው” አልነበሩም። ምናልባት ለእሱ እራሱ ብቻ ነው ሰው! የትክክለኛ ተሳዳቢ ባህርይ ሌሎችን ከሚሳደብበት ጉድለት አንፃር እራሱን አለመመዘን ነው:: የዲዮጋኖቹ ግን እራስን አንፅቶ በመመልከት ሰው ለመሆን መለኪያነት እራስን ማጨት ነው፡፡“ኮርማ ብሩ!”ዝም ብዬው የመሄዴ ምላሽ መሆኑ ነው:: በኮርማ ብሩ አፍራለሁ? የሥራ መግቢያ ሰዓት ቢረፍድም ጫማዬን ሳላስጠርግ. .

“ሸነኒቲ!!”አምስት ልጆች የነበሯት የሸኖ መስራች አፈ ታሪክ ናት፡፡ እና ሸነኒቲን ከእኔ ጋር ምን ያገናኛታል? ብሎ አሰበና መሳደቢያ አደረጋት?የአስታርቂኝ ማሪያም ደወል ተደጋግሞ ተደወለ፡፡ የአስካራ መቀስቀሻ ተደርጎ የነበረ ድምፅ ምናልባትም ርዝራዥ ሶልዳቶዎችን ያባንን ይሆናል:: የቤባንያ ወንድሞች ይኖሩ ይሆን? አሁንም ቤባንያን ያናገረ ሙሉ ሰው ይደበድቡ ይሆን? እነሱም እኮ በዚህ ጊዜ ሙሉ ሰው ናቸው፡፡ሊስትሮው፤ ድሮ እንጨት ተራ የምናገኘውን ሳንቲም የተቋጠረበት ጨርቅ መስሎ እስሬ ተቀምጧል፡፡ ሊያወራ ሲል ሌባ ጣቴን አፌ ላይ ገትሬ ዝም እንዲል አዘዝኩት።ዝም!ቀና ብሎ አየኝ፤ ፊቴ አልተፈታለትም:: ምን ያህል ተጨንቆ ይሆን? ወሬ በራሱ እንዳልተስማማ ምግብ በአፍ የመውጣት ግፊት አለው:: ያንን የሚለብቅ፣ ይቋቋመው ይሆን? የወሬ ማስወጣት ፍላጎት እንዴት ይቋቋመው ይሆንእኔ ቤባንያ ያለችበትን ሁኔታ የማወቅ ፍላጎቴን ተቋቁሜ ከመደወል አልታቀብኩም? ታዲያ? ሳይሞከር ይታወቃል። እኔ ከሄድኩ በኋላ ሳይናገር በመቅረቱ እራሱን እያደነቀ አዲስ የጨዋ ሰው ባህርይ ለማዳበር ይበረታታ ይሆናል።ኳ!ኳ!ኳኳ!“ማሰሪያውን ፈታኸው እንዴ? ለማስቦረሽ ነበር”“ምናለ ታዲያ? ይታሰራላ! ትናንት የሸኖ ሰው ሁሉ አመሰገነ አሉ፡፡˚ እራሴ በሸነቆርኳት የወሬ ቀዳዳ ሾለከ፡የሸኖ ህዝብ የቤተ ነዋይ ጥቅም ገብቶት እኔን አመሰገነ? ገንዘብ መቆጠብ፣ ከተገኘ ገንዘብ ተበድሮ ንግድ ማስፋፋት…“ጥሬ፣ ጥብስ፣ ቅቅል… በሽ በሽ ነበር አሉ፤ እኔ አላየሁም! ያዩ ሲነግሩኝ ነው::”እቺ ነገር ሽሙጥ ናት፤ የሽኖ ሰው የባንክ ምርቃት ሲባል፣ እንደ ሆቴል ምርቃት ምግብ የሚዘጋጅ መስሎት ነበር ማለት ነው::“በል ማሰሪያውን አንድ በልልኝና ልሂድ” አልኩት። ወሬ ሊቀጥል ሲል ሌባ ጣቴን የከንፈሬ ዘብ አድርጌ ገተርኩበት፡፡ዛሬ ሥራ የለም፤ ማለቴ የሸኖን ሰው በደንበኝነት መመዝገብና የባንክ ሒሳብ የማስከፈት ሥራ ይሰራል:: ይሁንና የደንበኛ አገልግሎት መኮንኖች ቦታ ቦታቸውን ይዘው ለአገልግሎት ይዘጋጃሉ። የተቀሩት ከተማውን በመዞር አዲስ ደንበኛ እያግባቡ ይመዘግባሉ፡፡የገንዘብ ቤት ኃላፊውና ሱፐርቫይዘሩ ተፈራርመው ገንዘብ ለማውጣት ሲጠባበቁኝ ደረስኩ። ሁሉም አሸብርቋል፡፡ ወደ ክፍሌ አመራሁ። የጠዋት ማብራሪያ አጭር ስብሰባ ያስፈልጋል፡፡ አጀንዳ ከመሳቢያ ውስጥ አውጥቼ እነሱ ወዳሉበት ዋና ክፍል ሄድኩ፡፡“ያላችሁበት ሆናችሁ አድምጡኝ። መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ። የዛሬ ሥራችን ግልፅ ነው፡፡ የሸኖ ህዝብ ወደ ባንካችን የመጣውን እዚሁ፤ ያልመጣውን ያለበት ድረስ እየሄድን አካውንት ማስከፈት ነው። ምክትል ሥራ አስኪያጁ የሥራ ድልድሉን ስላጠናቀቀ _ ያሳውቀናል። የገንዘብ ቤት ኃላፊውና ሱፐርቫይዘሩ የየራሳቸውን የምስጢር ቁጥር አሰባጥረው የተመጠነ ገንዘብ

አውጥተው ለከፋዮች ያከፋፍላሉ ይሄው ነው መልካም የሥራ ቀን ።”ሁሉም በያለበት ሲነቃነቅ ተሰማኝ፡፡በክፍሉ የሰራተኛ መቆጣጠሪያ መስታወት ውስጥ ሁሉም እንቅስቃሴ ይታየኛል። ሠራተኛው ሁሉ የባንክ ደንብ ተከትሎ ፅዱና አሸብራቂ ሆኗል፡፡ ግን ይሄ የባንክ ሠራተኞች የማሸብረቅ ደንብ ባንክ ከተመሠረተበት ህዝብ አንፃር መታየት የለበትም? የሸኖ ህዝብ አለባበስ ምን ይመስላል ብሎ ማጥናት፡፡ከዛስ?የባንኩ ሥራ አስኪያጅ ከሸኖ ባላባቶች አለባበስ መቅዳት ይኖርበታል፡፡ ምክትል ሥራ አስኪያጁ የጭቃ ሹሞቹን ብሉኮ ይደርባል። የተቀሩት የተራውን የሸኖ ህዝብ የዘወትር አለባበስ አስመስለው ያስተናግዳሉ፡፡ እንዲህ ያለው አለባበስ ጥቅሙ የሸኖ ህዝብ የባንኩን ሠራተኞች _ አሸብራቂነት አይቶና አነስተኛነት ተሰምቶት እንዳይሸሽ ማድረጉ ነው።ይሄን ጥናት ብዬ ለበላይ የባንክ ኃላፊዎች ባቀርብ የሚንጫጫው መአት ይሆናል:: ምክንያታቸውን ሳያቀርቡ ጫ! ጫ !. የጫጫ ተቃውሞ።አንድ ሰው ገብቶ ሳይቆይ ሲወጣ ተመለከትኩ። ወጥቼ ቴለሯን አናገርኩ።”ፎቶ ስላልያዙ እንዲያመጡ ነግሬአቸው ነው::” ከንፈሯ አብጦ እና ዳርዳሩን ተኩላው ሲታይ ፊቷን ባለሥስት አይን አስመስሎታል፡፡”ፎቶ የመጨረሻው ጥያቄያችን ይሁን ሙሉ መረጃቸውን ተቀብላችሁ ደብተሩን አስወጡላቸው ፣ የሚቆጥቡት ካላ ይሁን፤

ይቆጥቡ እና ፎቶውን እንዲያመጡ ንገሯቸው:: በፎቶ ምክንያት አትመልሱ፡፡” አልኩ፡፡ባለሦስት አይኗ ጭንቅላቷን ወዘወዘች:: “ለመስክ ሥራ ለተሰማሩትም ይሄንኑ ንገሩ”

“እሺ” በሦስተኛ ዓይኗ

Related Articles

ቤባንያ ገፅ ፰

“አውርድ አንተ ጅል ትላለች ብዬ ጠበኩ ዝም አለች የእነሱን ሠፈር ርቀን ሄደናል፡፡ የጉልት ገበያ በአመሻሽ ግብይት እንደመሞቅ ብላለች፡፡ የዕለት ፍጆታዎችን ለመሸጥ ቁጢጥ ቁጢጥ ያሉ ሴቶች...

ቤባንያ ገፅ ፯

ክፍል 4 ለማና ወዳጄ ልቤ ቤባንያ የክልስ መልክ አላት፡፡ ገና ዘጠነኛን እንዳለፍን እኛ ክፍል ቁጭ ብላ አገኘኋት። ልቤ “ባትጋሩኝ አለ ተሽቀዳድሞ:: እንደአልማዝ' እንደዕንቁ፣ እንደ...

ቤባንያ ገፅ ፮

“ታዲያ ምን ሆኖ ነው? እቃጠለኝኮ ተቃጠልኩ ውሃ የለም?” እኔ እቀጥላለሁ፡፡ "ከገንዘብ ይልቅ የዕታ ለዕቃ ልውውጥ እንደሽኖ ላሉ ነባር ከተሞች ውጤታማነቱ ተረጋግጧል፡፡ (ማነው...

Comments

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *