ቤባንያ ገፅ ፰

December 23, 2023

“አውርድ አንተ ጅል ትላለች ብዬ ጠበኩ ዝም አለች የእነሱን ሠፈር ርቀን ሄደናል፡፡ የጉልት ገበያ በአመሻሽ ግብይት እንደመሞቅ ብላለች፡፡ የዕለት ፍጆታዎችን ለመሸጥ ቁጢጥ ቁጢጥ ያሉ ሴቶች ይታያሉ። እንጨት፣ ቅጠል፣ ጎመን፣ አይብና የስኒ ቅቤ ይታየኛል፡፡

ቤባንያ ናፍቀሽኛል አልኳት፡፡ ዝም አለችኝ:: የባዕድ መልኳ በባህል ክንብንብ ተከቦ ሲታይ ልዩ ህብር ፈጥሯል። ግማሽ ነጠላዋን ግማሽ ጉንጯን ሳምኳት
ዝም!

ምን ሆናለች?

ህልም እየመሰለኝ ሄደ፡፡ ቆይታ: ቆይታ

“አብዝተሽዋል፤ ወንድሞቼ ይገድሉሻል” አለችኝ::

“ይግደሉኝ!”

“እ…” ብላ አፏን አሞጥሙጣ ወደ ፊቴ አስጠጋችና።
“እንቺማ ጅል ሳትሆኚ አትቀሪም”
“ነኝ”
“ወንድሞቼ ሲይዙሽ እንደሱ በያቸው”

የጣሊያን ጦር በፊቴ ተሰልፎ አለፈ። ከጎኔ ብትሆን መንገዱን እሷ እየመራች ነበር፡፡ ከጉሊት በጋፈሮ አድርገን ወ ኮረማሽ ተሻገርን፡፡ የአፄ ምኒልክ የጥይት ግምጃ ቤት ነበር ይሉታል ከፍታው ቦታ እንደመጋረጃ ተጋልጦ ድፍን ቡልጋን እስከ አፋር በረሃ ድረስ ያሳያል። አንዳንድ ወጣቶች ጥንድ፣ ጥንድ ሆነው በመጠጋጋት ተቀምጠዋል። ፈቀቅ ብለን እኛም ተቀመጥን።

“ያ ከሰም በረሃ ነው፣ ቡልጋ” የጠቆመችኝ በአገጯ ነው። ጭራሽ ወደ ጠቆመችኝ ቦታ አላየሁም:: በነጠላ የተከበበ ፊቷ የአመሻሽ ጀምበርን ብርሃን ተቀብሎ ያበራል፡፡

የኛ አያት የተወለደው፤ እዛ አሳግርት የሚባለው ቦታ ነው:: ዓለሙ ሚካኤል ይባላል። የከበደ ሚካኤል ወንድም ነው:: ከበደ ሚካኤልን ታውቃለህ?”

“እዚህ ሽኖ ውስጥ ናቸው?”

ከት ብላ ሳቀች፡፡ ሳቋ ውስጥ እውነተኛው “ጅል” የሚል ስድብ ጎማሁ መሰለኝ፡፡

“ከበደ ሚካኤል፣ ፋኖስና ብርጭቆን አላነበብክም?”

“አላነበብኩም” ማለት እንዲህ ይመራል?

“አባቴ ሁሌም “እስኪ የአጎቴን ፅሁፍ አንብቡ ልጆች’ ይላል:: ያስነብበናል “

ዝም አልኩ፡፡

በጣም ተጠግታኝ እንዳቅፋት አድርጋ እንደ ክንብንቧ የፊቷ ይዞታ ጋር የማይገጥም ግጥም አነበበች።

“አንድ የፋኖስ መብራት በግብሩ የኮራ

እንዲህ ሲል ተጣላ ከብርጭቆው ጋራ:: እኔ ነኝ መብራቱ ብርሃን የምሰጥ፤

ጨለማን አጥፍቼ የምገላልጥ።”

የምታነበንበው ውሉ ሳይገለጥልኝ፤ የፃፈው የአባቷ አጎት ብቻ እንደ ድግስ ቆጥሬ ሰማኋት፡፡
“…..
ልሂድልህ ብሎ ሲለቅለት ቦታ

ከጎን የነፈሰ የንፋስ ሽውታ መጣና መብራቱን አጠፋው ባንድ አፍታ፡፡ አጭር እየሆነ ተመልካችነቱ መለየት አቅቶት ጥቅሙን ከጉዳቱ፡፡ እወቁኝ፤ እወቁኝ እያለ ሲነሳ ሰውም እንደዚሁ ያመጣል አበሳ።”የሆነ ነገር በተላላፊ ሲነካኝ ታወቀኝ።“እስኪ፣ እስኪ የመጨረሻውን ድገሚልኝ” አልኳት፡፡ በፍቅር አይን አይታኝ”ጅልኮ አይደለሽም፤ ጭንቅላት አለሽ፡፡ ዋናው ነጥብ እንዳልከው የመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞች ላይ ነው ያለው::”ደገመችልኝ።”እኔን የሚመለከተኝ መሰለኝ፡፡” አልኳት”ሁላችንንም ይመለከታል”ዝም ተባብለን ወደ ጀንበር መጥለቂያዋ አገር አተኮርን፡፡ ከበደ ሚካኤል እናንተን ይመስላሉ?”“አዎ፣ አባቴ እኔን፤ ቁጭ አጎቴን ትመስያለሽ፣ አይ ዘር ይላል፡፡ምን ቢያሽሞነሙኑት እውን ህልምን አያክልም። እውነት ቁጠባ ይበዛዋል:: የተቻለን ያህል ማካሄድን አይፈቅድም። ቤባንያ ብትፈቅድ እንኳ አልስማትም። በእውኑ ዓለም ውስጥ ፍቅር የሚጎመራበት የራሱ ጊዜና እንክብካቤ ይፈልጋል፡፡ አስሬ እውንን ብንጠላ፤ ጠልተን ብናፈርሰው ህልምን አይተካም።

ቤባንያን ከጎን በኩል እንደተከናነበች ሳያት ቤተክርስቲያን ያለሁ ሆኖ ተሰማኝ። እርሷ ያለችበት ሁሉ ይቀደሳል? መውደዴ ምን አስመስሎ እያሳየኝ ነው? ላመልካት ይሆን?ያቀፍኩበትን እጄን አንስቼ ጭኗን ፈልፍዬ ተንተራስኩት፡፡ ይቺ ናት ቤባንያ፡ ከስር ወደ ላይ ሲመለከቷት፣ ፀጥ ባለ ፊት ቁልቁል ስትመለከተኝ፣ ይሄ ሁሉ ዋጋ እንዳለው አውቃለሁ:: እንደ ደቻሳ በአንድ ቀን ጉሸማ ጥያት እጠፋለሁ? ዓይኖቼን አቃርንባታለሁ? ከውስጤ እነቅላታለሁ?……ጥቂት ለማይባሉ ነገር ግን ጥቂት ለሚመስሉ ግዜያት፣ እኔና ቤባንያ ሸኖን እያካለልን ተገናኘን፡፡ ዘመዷ ፀሐፊው ከበደ ሚካኤል አብረውን ያሳልፋሉ፡፡ ብዙ ማብስያ ግጥሞችን ከእርሳቸው እየዘረፈች ባፍ ባፌ ትለኛለች፡፡”ሰዎች ከሰው ጋራ ሽሪክ ስትሆኑ፣ ዐቅማችሁን በፊት አይታችሁ መዝኑ::የከበደ ሚካኤልን ዘዴ የነቃሁበት መሰለኝ፡፡ አይኔን ጨፍኜ አውቶቡስ እንደተሳፈረ ሁሉ ብዙ የግጥም ፌርማታዎችን አልፍና ድንጎት መውረጃዬ ሲደርስ ይታወቀኛል። ብዙ ጊዜ ግጥሙ ሲጀመር በማስረጃ ይሆንና መጨረሻ ላይ የተፈለገው ምክር ይመጣል፡፡ከትምህርት ቤት በጓሮ በር ከወጣሁ ቤባንያ እቤት ደርሳ፤ ነጠላ ደርባ ትመጣለች:: መሄጃችንን የምትወስነው እሷ ናት፡፡ “እዚህ እንረፍ እስክትለኝ ድረስ መሄጃችንን እኔም አላውቀው።“ጆቢር ሜዳ እንሄዳለን። በውስጡ ብዙ አረንቋ ቦታዎች አሉ:: ‘ጨፍ! ጨፍ!” እያደረግን መሃል ስንደርስ አንዲት ደረቅ ቦታ ላይ ቁጭ ትላለች፡፡ ሱሪዬ በቀጭን ጭቃ ጫፍ ጫፉን ተጠልፏል፡፡ ጭጋጉ እንደከንፈር ወዳጆች ነጠላ መጥቶ እላያችን ላይ ይሰፍራል፡፡

ቀይ መልኳ ውስጥ የተቀበረው ነጭ ጥርሷ ብርሃን እየፈለቀ ለአይኒ ይደርሳል::በዚህ አትጣጫ ዝም ብለህ ከሄድክ ትላለች ቤባንያ በአገጯ ልብ ያላልኩትን ገጥ እያመለከተች። “የብላቴና ጌታ ኀሩይ ወልደሥላሴ አገር ነው:: መረሸት ይባላል፡፡” ማናቸው?ፀሐፊ ናቸው፡፡”እሳቸውም አጎትሽ ናቸው?”“አይ፣ ‘ወዳጄ ልቤ’ የተባለ መጽሐፍ አላቸው፡፡ ‘ስኳርና ወተት’፣ ‘ደስታና ክብር’፡ ‘በዕድሜ ልሰነብት ሁሉን ለማየት የተባሉ፤ ሌሎችም ብዙ መጽሐፍት አሏቸው።'””እንደ ከበደ ሚካኤል ይጥማል?’“እዎ፣ አባቴ በተራ በተራ ያስነብበናል፡፡”“ስማቸው ግን እረጅም ነው:: እስከነ ቅድመ አያታቸው ነው የሚጠሩት?’ጅል’ የሚለውን ሳቅ በጭጋግ መካከል ለየሁት፡፡”ብላቴን፤ ጌታ የክብር ስማቸው ነው፡፡ ኅሩይ የራሳቸው ወልደሥላሴ የአባታቸው ሥም::”መጠየቄ አለማወቄን የሚያሳብቅ መሪ ኮከብ ሆኖ አገኘሁት ግን ቤባንያ መልስ ከሰጠችኝ በኋላ ጭኗን እንደተንተራስኩ አጎንብሳ አፌ ላይ ሳመችኝ፡፡ መጠየቄ፣ አለማወቄ የመሳሜ መሪ ኮከብ ሆና አገኘሁት:: አንገቷ ላይ ተጠምጥሜ ልቀር ስል ነጠቀችኝ።አፈርኩ።“እኛኮ ታድለናል” አለች፡፡

Related Articles

ቤባንያ ገፅ ፲፪

“ቋ!ቋ!ቋ!ቋ!…" “ምን ሆንሽ አመቴ!" አንድ ጥግ ላይ ተጎዝጉዞላት የተኛች አሮጊት ናት፡፡ “ምን ሆንሽ?” “ጥለውኝ ሄዱ" ባለፈውም የሰጠችው ምክንያት ነው:: “ጅብ ሊያስበሉኝ እዚህ...

ቤባንያ ገፅ ፲፩

በመጀመሪያ ኬኦስ ነበረ፣ የማይጨበጠውና ዉጥንቅጡ ኬኦስ የረጋቸውን ምድር(ጂኦን) ወለደ:: "እንዴት?" አይባል የሚያሰኘው የእኔ ከምንም ውስጥ መገኘት ነው፡፡ ሃይፒሪዮን ፀሐይን፣ ጨረቃንና...

ቤባንያ ገፅ ፲

ኩራዙ በየቀን ብርሃን ተውጣ ስንጥር የመሰለ ጨረር ታግለበልባለች፡፡ ዝም ብዬ ቆምኩ፡ “ሃሎ ሚስተር ባንከር" አለኝ ድምፁ ብቻ ብቅ ብሎ ዝም አልኩት፡፡ "ለከተማህ መቅሰፍት ይዘህ መጣህ?...

Comments

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *